Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ትብብር ዙሪያ ከሀገሪቱ አምባሳደር ጋር መከሩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በኢትዮጵያ ከዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ዳረን ዌልች ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ዘመናትን የተሻገረው የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩ በውይይቱ ላይ ተንጸባርቋል ብለዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለይ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አተገባበር፣ በትምህርትና በጤና ዘርፍ የነበሩ የትብብር ማዕቀፎች እጅግ ስኬታማ መሆናቸውንና ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ቁርጠኛ መሆናችንን ገልጸናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በርካታ የሪፎርም ተግባራትን በመፈፀም ሁለተንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየተጋች መሆኗን ገልጸው፥ ከነዚህ መካከል የተቋማት ግንባታ አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ረገድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ምህዳሩን የሚያሰፉ ርምጃዎችና የተቋም ግንባታ ስራዎች በሰፊው የተሰሩ ሲሆን፥ የምርጫ ቦርድ ነፃና ገለልተኝነት እንዲሁም የሲቪል ሰርቪስ መዘመን የሚታዩ ለውጦች ተገኝተውበታል ብለዋል።

ለአብነትም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋፋት ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዮችን እርካታ በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በቀጣይ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚረዳ መልኩ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የልምድ ልውውጥ መድረኮችና የትብብር ማዕቀፎች እንዲመቻቹ ከመግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡

Exit mobile version