Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የሲንጋፖር ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ውይይታችን በሁለቱ ሀገሮቻችን መካከል ያለንን ግንኙነት ለጋራ ነጋችን ወሳኝ በሆኑ መስኮች በጋራ ለመሥራት በምናደርገው ጥረት ውስጥ አንድ ጠቃሚ ርምጃ ነው ብለዋል።

በተለይም በክሂሎት ልማትና በካርበን ብድር ትብብር ያደረግናቸው የመግባቢያ ስምምነቶች ጽኑ እና ለነገው ገበያ ዝግጁ የሆኑ ሠራተኞችን ለማፍራት ብሎም በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ ዘላቂ፣ ዝቅተኛ ካርበን የሚያወጣ እድገት ለማረጋገጥ ያለንን የጋራ አቋም የሚያንፀባርቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከሲንጋፖር ጋር ይህን የወዳጅነትና የትብብር ጉዞ በጋራ በመቀጠላችን ክብር ይሰማናል ነው ያሉት።

በላቀ ተግባራዊ ትብብር ንግድና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት፣ ዘመናዊ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስን በማልማት፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት፣ በገንዘብ ልውውጥ ቴክኖሎጂ፣ በሳይበር ደኅንነትና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፎች ያለንን ትብብር ለመጠቀም እጅግ ሰፊ አቅም አለን ብለዋል።

Exit mobile version