አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቡና ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ስኬት ታሪካዊ እና ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅምን የፈጠረ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ ቡና አምራቾች፣ ላኪዎች እና የዘርፉ ባለድርሻዎች በተገኙበት ሀገር አቀፍ የቡና ኤግዚቢሽንና እውቅና መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ 470 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 2 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር አግኝታለች ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 600 ሺህ ቶን ቡና በመላክ ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ለማግኘት መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡
የቡና ምርታማነትንና ጥራት የሚያሻሽል ኢኒሼቲቭ ተቀርጾ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ9 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል፣ ከ700 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ ያረጁ ቡናዎችን ማደስ እና ሌሎች ስራዎች የቡና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል 200 እና 300 ሺህ ቶን ቡና በዓመት ለማምረት የነበረውን ችግር መታለፉን አስታውሰዋል።
ምርታማነታችን ለብዙ ጊዜ ዥዋዥዌ ሲጫወትበት ከነበረው 6 እና 7 ኩንታል በሄክታር በአሁኑ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ 9 ኩንታል በሄክታር ማምረት ችለናል ሲሉም ገለጸዋል፡፡
ይህም በተለያዩ ክልሎች በሞዴል አርሶ አደሮች 15 እና 20 ኩንታል በሄክታር እየተመረተ ያለውን ሳንጨምር ነው ብለዋል፡፡
ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን በጥቂት ባለሀብቶች የተጀመረው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ቡና የማምረት ተግባር በሄክታር እስከ 60 ኩንታል ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።
ይህም ሀገራችን በቅርቡ ቁጥር አንድ ከሆኑት ቡና አምራች ሀገራት መካካል ለማድረስ የወጠነችውን ማሳካት እንደሚቻል አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫችን ቡናን በጥሬው ብቻ ሳይሆን እሴት በመጨመር የተሻለ ገቢ እና የተሻለ ዕድል መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መሆን ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ከቡና በተጨማሪ የሻይ ልማት ተስፋ የሚሰጥ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በለይኩን ዓለም

