አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዘዥ ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን የተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ኢትዮጵያና አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት መክረዋል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚህ ወቅት ÷ ሁለት ሀገራት ወታደራዊን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ለበርካታ ዓመታት በትብብር እየሠሩ መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷ ለሠላማዊና ኢኮኖሚዋን ለመገንባት መሆኑን ያብራሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ ከአሜሪካ ጋር ያለው ወታደራዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ አልሸባብን ለማዳከምና የሽብር ሴራውን ለማክሸፍ የምትወስደውን የኃይል ርምጃ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
ጄነራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ በቀጣናው ፀጥታን ለማስፈን እየተጫወተች ያለችውን ሚና አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ሽብርተኝነትን በጋራ የመዋጋት ሥራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሠላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸው ÷ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ብትመጣ የበለጠ ለቀጣናው ሠላም ትሠራለች ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ በኩል ያሉ ፍላጎቶችንና በቀጣናው ሠላምን ለማረጋገጥ ስለያዘቻቸው ዕቅዶች ከዋሺንግተን ዲሲ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚመክሩ መናገራቸውንም የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
በመላኩ ገድፍ

