Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአፍሪካ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ቀጣናዊ ትብብር ወሳኝ ነው – አቶ አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥና የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ቀጣናዊ ትብብር ወሳኝ ነው አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፡፡

ሚኒስትሩ በሞሮኮ ራባት እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ባደረጉት ገለጻ፥ መሰረተ ልማት፣ ቴክኖሎጂና የገበያ እድል በአህጉሪቱ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ትብብር ቅድሚያ እንደምትሰጥና የውጭ ጉዳይና የኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ማዕከል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሀገር ውስጥ ሪፎርሞችን ከአህጉራዊ ማዕቀፎች ጋር በማጣጣም ለቀጣናዊ ትብብር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፥ ለአብነትም በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና፣ በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኢኮዋስ) እና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ውስጥ ያላትን ተሳትፎ አንስተዋል፡፡

በአፍሪካ የግሉን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ ቀጣናዊ ትብብር ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ የተጣጣመ ፖሊሲን መተግበር፣ የገበያ ትስስርን መፍጠርና ድንበር ተሻጋሪ መሰረተ ልማቶችን መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ከተለያዩ ሀገራት የኢንቨስትመንት ህጎች ጋር የተጣጣሙ ህጎችን በመተግበር፣ ዘመናዊ የጉምሩክ ስርዓትና ዲጂታል የንግድ ስርዓት በመዘርጋት በትኩረት እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክን የመሳሰሉ አጋር ተቋማት በሚያደርጓቸው ድጋፎች የቀጣናውን ሀገራት በኃይል አቅርቦትና በዲጂታል አሰራር ለማስተሳሰር እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በሎጅስቲክስ እንዲሁም በአገልግሎትና በአምራች ዘርፎች ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ቀጣናዊ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋትና በንግዱ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት አህጉሪቱን ተወዳዳሪ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የአፍሪካ ሀገራት፣ የልማት ፋይናንስ ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ አጋሮች በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version