Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ኮፕ-32 ጉባኤን ለማስተናገድ መመረጧ የታዳሽ ኃይል ልማት ቁርጠኝነቷን የሚያረጋግጥ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ ለማስተናገድ መመረጥ የታዳሽ ኃይል ልማት ትግበራ ቁርጠኝነቷን የሚያረጋግጥ ነው አሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)።

ሚኒስትሩ እንዳሉት ÷ በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢኮኖሚ ግንባታ የውሃ፣ የፀሐይ፣ የነፋስ፣ ጂኦተርማልና መሰል የኃይል አማራጮች ወሳኝ ሚና እየተወጡ ነው፡፡

በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን በፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ባልተዳረሰባቸው የገጠር መንደሮችና ከተሞች የፀሐይ ኃይል ተጠቃሚነት ለማሳደግም ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል የልማት ስኬትም የካርበን ልቀትና የአየር ንብረት ለውጥ ስጋትን በመቀነስ ዓለም አቀፍ እውቅና እያስቸራት መሆኑን አብራርተዋል።

የበለጸጉ ሀገራት ዕድገታቸውን ለማረጋገጥ የተጓዙበት መንገድ በካይ ጋዞችን በመጠቀም በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ዓለምን ዋጋ እያስከፈሉ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የሚገነቡ የታዳሽ ኃይል አማራጭ መሠረተ ልማቶችም በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እየተፈተነ ለሚገኘው ዓለም ከፍተኛ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማት ግንባታም የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ልማት ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን በማጠናከር ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤዎችን የምታስተናግድበትን ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።

በብራዚል በተካሄደው መድረክ ኢትዮጵያ ኮፕ-32 ጉባዔን ለማስተናገድ ስትመረጥ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስመዘገበችው ስኬት ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ኮፕ-32 ጉባኤን ለማስተናገድ መመረጧም በታዳሽ ኃይል አማራጭ፣ አረንጓዴ አሻራና በታዳሽ ኃይል ልማት ላስመዘገበችው ስኬት ዕውቅና የሚሰጥ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ የውሃ ሃብቶችን ደኅንነት በመጠበቅና የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከደለል በመታደግ ወሳኝ ድርሻ እየተጫወተ ነው ብለዋል።

Exit mobile version