አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አፍሪካ ሰላም የሰፈነባትና የበለጸገች እንድትሆን ተቋማት በፍትህ ላይ ተመስርተው ሊሰሩ ይገባል አሉ፡፡
4ኛው የአፍሪካ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤቶች ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የአፍሪካ የረዥም ጊዜ መሻት የሆነውን ልማት፣ ብልጽግና እና ትብብር ለማሳካት ህገመንግስታዊነትና ውጤታማ የሀገረ መንግስት ግንባታ ቁልፍ ተግባራት መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
ሰላም የሰፈነባት፣ የበለጸገችና አንድነቷ የተረጋገጠ አፍሪካን ለመፍጠር ተቋማት በፍትህ ላይ ተመስርተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውና ዜጎች በመረጧቸው መንግስታት ብቻ ሊተዳደሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት ህግ ከማውጣት ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር፣ ተጠያቂነትን ለማስፈንና መሰረታዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።

