አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ብሔራዊ ጥቅሙን ማስጠበቅ ያልቻለ ሀገር እንደ ሀገረ መንግስት መቀጠል አይችልም አሉ፡፡
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፥ ብሔራዊ ጥቅም ለሀገረ መንግስት አንዱ ወሳኝ አንጓ ነው፡፡
ብሔራዊ ጥቅም ካልተከበረ ሀገራዊ ክብር እንደማይኖር አንስተው፥ የባህር በር ጉዳይም ከሰላምና ደህንነት አንጻር የብሔራዊ ጥቅም ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ሀገር ሰላም እና ደህንነቷ እንዲረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷና ጥቅሞቿ እንዲከበሩ እንዲሁም ሀገረ መንግስቱ የተረጋጋ ሆኖ እንዲኖር የሚያስችል ስርዓት የመዘርጋት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ አስተሳሰብ፣ በርዕዮተ ዓለም፣ በአመለካከት፣ በአቋም እንዲሁም በሌሎች መመዘኛዎች ልዩነቶች ሊኖሯቸው እንደሚችል አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ምንም አይነት ልዩነት ቢኖር በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ አንድ በመሆን ጥቅሞቻችንን በአንድነትና በተባበረ መንፈስ ማስከበር አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ይህ ካልሆነ ብሄራዊ ጥቅሞቻችንን አሳልፈን እንሰጣለን፥ እንደ ሀገር ለመቀጠል እንቸገራለን ነው ያሉት፡፡
በብርሃኑ አበራ
የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር የነበራቸውን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ፡- https://www.youtube.com/watch?v=AnRAmc-DkNc

