Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሀገራት ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል – የተባበሩት መንግስታት

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ሀገራት ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን የልማት ስትራቴጂዎቻቸው አካል በማድረግ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል አለ፡፡

ዩኤንዲፒ ባወጣው ሪፖርት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቀድሞ መገኘት ካልተቻለ በቀጣይ በሀገራት እድገት መካከል ያለውን ልዩነት ይበልጥ እንዲሰፋ ያደርጋል ብሏል፡፡

ሀገራት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅማቸውን ለማሳደግ ቀድመው መስራት ከቻሉ ይህንን ልዩነት ማጥበብ የሚችሉበት እድል መኖሩን ጠቁሟል፡፡

በዚህም ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ የዲጂታል ክህሎትን መገንባት፣ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ማጠናከር እንዲሁም የዲጂታል መሰረተ ልማትን ሊያስፋፉ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

ሀገራት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፕሮግራሞቻቸው ጎን ለጎን በተለይም የወጣቶችንና ሴቶችን የሰው ሰራሽ አስተውሎት እውቀት ለማሳደግ የሚያግዙ ሀገራዊ ፕሮግራሞችን ቀርጸው እንዲሰሩ ዩኤንዲፒ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል፡፡

ጠንካራ ዲጂታል መሰረት ያልገነቡ ሀገራት ከቴክኖሎጂው የሚገኘውን እድል በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚቸገሩ ጠቅሶ፥ የኮምፒዩተር ክህሎት፣ የመረጃ መሠረተ ልማትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል መንግስታት የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዜጎችን የሥራ እድል የሚዘጋ እንዳይሆን፣ አካታች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትንና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም መረጃዎች ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለመቆጣጠር መመሪያዎችን ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝቧል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version