Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሰላም መንገድ ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል – የሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰላም መንገድ ሁሌም ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል አለ የሰላም ሚኒስቴር፡፡

ሚኒስቴሩ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ በሰጠው መግለጫ፤ መንግሥት ለገጠሙን ችግሮች ውይይት እና ንግግርን ብቸኛ አማራጭ መንገድ መሆናቸውን እና ለዚህም ቁርጠኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ማሳየቱን ገልጿል።

ቀድሞ የኃይል አማራጭን ተጠቅመው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ይህንን የሰላም አማራጭ በመምረጥ ወደ ሰላማዊ መንገድ ሲመጡ መንግሥት ከግማሽ ርቀት በላይ በመሄድ በመቀበል ቁርጠኝነቱንም አሳይቷል ብሏል።

ይህ መንገድ በሀገሪቱ የሰላም፣ የፍትሐዊ እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስችል ብቸኛው አማራጭ መሆኑ የመንግሥት እምነት እንደሆነም አመላክቷል።

በዚህ አጠቃላይ መነሻ በአማራ ክልል ቀድሞ የኃይል አማራጭን ተጠቅመው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት የኃይል አማራጭ ለሕዝባችን ሰላም እና ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት ፋይዳ እንደሌለው በማመን ወደ ሰላማዊ መንገድ በመምጣት ድፍረት ያለው ውሳኔ አድርገዋል ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው።

ይህ የሰላም አማራጭ ሁላችንንም አሸናፊ ስለሚያደርግ ሚኒስቴሩ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና ለአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ለወሰዱት ቆራጥ ርምጃ ያለውን አድናቆት ገልጿል።

በሌላ በኩል አሁንም ቢሆን የትኛውም ጥያቄ ያለው አካል ለጥያቄው መልስ ለማግኘት ብቸኛው መፍትሔ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገውን መነጋገር እና መወያየትን መሠረት ያደረገ የሰላም መንገድ መሆኑን በማመን ኋላ ቀር የሆነውን የኃይል አማራጭ በመጠቀም የሚንቀሳቀሱ አካላት ተመሳሳይ የሰላም መንገድን እንዲመርጡ ጥሪ አቅርቧል።

Exit mobile version