አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ነው አሉ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ምክትል ዳይሬክተር ናይጅል ክላርክ ጋር በመሆን በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአይኤምኤፍ ያገኘችው የልማት ድጋፍ በሀገሪቱ ታሪክ ትልቁ የኢኮኖሚ ትብብር ነው፡፡
በአይኤምኤፍ ድጋፍ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላላው የኢኮኖሚ ልማት እንዲሁም ተግባራዊ እየተደረገ ስላለው የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልጸው፤ ሀገሪቱ የተሟላ የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረጓ ሁለንተናዊ እድገትና ለውጥ ማስመዝገቧን አስረድተዋል፡፡
ምክትል ዳሬክተሩ በበኩላቸው፤ ተቋማቸው የኢትዮጵያን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
መንግሥት በማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያው ያስመዘገበው ውጤት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው፤ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት መዋቅራዊ ሽግግር እገዛ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጎልበትና ሁለንተናዊ ልማትና እድገት እውን እንዲሆን የሚሠጠው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ገልጸዋል።

