አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በወታደራዊ ልምድ ጥልቅ ጥናት ላይ ተመስርቶ ‘የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ’ በሚል ርዕስ በአምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ የተፃፈ መጽሐፍ ተመርቋል።
በመጽሐፉ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አመራሮች ተገኝተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያ የተሰነደ የፀረ ሽምቅ ውጊያ ማኑዋል የነበራት ቢሆንም የተሻሻለ እንዳልነበረ ጠቅሰዋል።
‘የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ’ መጽሐፍ ዘመኑን የሚመጥንና ለጦር መሪዎች ማስተማሪያነት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ይህንን ጠቃሚ መጽሐፍ ለአንባቢያን በማበርከታቸውም ምስጋና ማቅረባቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
አምባሳደር ጄነራል ባጫ ደበሌ በበኩላቸው÷ ቀደም ሲል የሀገር ጦር መሪዎች የሚጽፉት መጽሐፍ ታሪክ ላይ እንደሚያተኩር አስታውሰዋል።
በ187 ገፆች የተቀነበበውና በአምስት ምዕራፎች የተከፋፈለው የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ጥበብ መጽሐፍ ሳይንሳዊ ይዘቶችን ያካተተ ነው ብለዋል።
መጽሐፉ ስለሽምቅ ውጊያ ዳራና ልምድ የፀረ-ሽምቅ ውጊያ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች፣ የሸማቂና የአሸባሪ ቡድኖች ባህሪ፣ የፀረ-ሽምቅ ውጊያና የፀረ-ሽምቅ ግብረ-ኃይል ዝግጅትን ምንነት የሚገልፅ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

