አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች መንግሥት የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በማዳመጥ ምላሽ እየሰጠና ሀሳቦቹን በእቅድ በማካተት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው አሉ።
በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች “የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
በኮልፌ ቀራንዮ በተካሄደው መድረክ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሀይ ጳውሎስ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ እንዲሁም ሌሎች የስራ ሀላፊዎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ሀላፊ ሊድያ ግርማ ከዚህ ቀደም ከህብረተሰቡ በተነሱ ጥያቄዎች ላይ የተሰጡ ምላሾችን እና ቀጣይ የልማት ስራዎች ላይ ባደረጉት ገለጻ፤ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት የህግ ማዕቀፎች መሻሻላቸውን፣ የተቋማት ሪፎርም እና ዲጂታል አሰራሮችን ተግባራዊ በመደረጋቸው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሲስተዋሉ የቆዩ ብልሹ አሰራሮችን እየተቀረፉ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመፍታት የምርት አቅርቦት እንዲሻሻል መደረጉን እና በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ጠቁመው፤ መንግስት የሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ ናቸው ብለዋል።
በቀጣይም ብሔራዊ ፕሮጀክቶች የሆኑት የጉባ ብስራቶችን ጨምሮ በርካታ የልማት ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች መንግስት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸውን አስደናቂ ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ሀገራዊ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የተማሪዎች ምገባ እንዲጠናከር፣ የጤና ተቋማት ግንባታ እንዲስፋፋ እና የኑሮ ውድነትን ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ከመሰረተ ልማት እንዲሁም ከውሃ እና ከኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጥ ጋር ያሉ ተግዳሮቶች እንዲፈቱም ጠይቀዋል።
መድረኩ ለበለጠ መግባባት እና ስራ ይጠቅማል ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሀላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምጸሀይ ጳውሎስ፤ አሁንም የላቀ ስኬት ለማሳካት በጋራ በህብረት መቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የመንግሥት ትልቁ እይታው ህብረተሰቡን አዳምጦና የፍላጎቶቹን ጥያቄዎች በእቅድ አካቶ ምላሽ እየሰጠ እንደሚሄድ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በቱሪዝም እንዲሁም በዲጂታላይዜሽን ላይ ኢኒሼቲቮች ቀርጸው በመተግበራቸው በርካታ ውጤቶች እንደተመዘቡ ገልጸዋል።
ከፊት ለሚጠብቁን ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ በውይይቱ የተነሱ ሀሳቦች በየደረጃው እንደሚፈቱም አረጋግጠዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በበኩላቸው፤ ህዝብን በማሳተፍ እንዲሁም ልማትን ብሔራዊ አጀንዳ በማድረግ በርካታ ድሎች መገኘታቸውን ጠቁመው፤ ለልማት ስራዎች የህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የህብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመፍታት መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ የህዝብን አንድነት እና አብሮነት ሊሸረሽሩ የሚሰሩ አካላትን መታገል እንደሚገባ ነው አጽንኦት የሰጡት።

