Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ይፋ አድርጓል።

በዚህ መሰረት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መሆኑን አስታውቋል።

ቦርዱ ዘንድሮ የሚካሄደውን የ7ኛ ሀገር አቀፍ ምርጫ እየተከናወኑ የሚገኙ ዝግጅቶችን እና የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ የምርጫ ጽ/ቤቶችን የማደራጀት ስራ ከየካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 15 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥቅምት 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕውቅና እንደተሰጣቸውም አስታውሰዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳቦቻቸውን ለመራጩ ህዝብ እንዲያሳውቁ ለማስቻል ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው፤ በዚህም 56 ፓርቲዎች የሙከራ ክርክሮችን ማካሄዳቸውን አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የመራጮች እና የእጩዎች ምዝገባን ቦርዱ ባለማቸው ሶፍትዌሮች በመታገዝ ለማከናወን ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም መራጮች ዲጅታላይዝ በሆነ መንገድ በስልካቸው፣ በዌብሳይት እና በምዝገባ ጣቢያዎች በታብሌት መመዝገብ እንደሚችሉ እና ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በማንዋል መንገድም ምዝገባዎች እንደሚከናወኑ ነው የጠቆሙት።

እንዲሁም የእጩዎች ምዝገባን በዲጅታላይዝ መንገድ ለማከናወን ለፓርቲዎች ተወካዮች ስልጠናዎች መሰጠቱን አብራርተዋል።

የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎችን የመመልመል ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ እና የጽሁፍ እና የቃል ፈተና በመካሄድ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የጸጥታ ሁኔታዎችን የመገምገም ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ይፋ የተደረገረገው የምርጫ ሰሌዳም ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበረሰቦች ጋር በመወያየት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ይፋ በተደረገው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ላይ ድምጽ የሚሰጥበት ቀን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሆነ ተመላክቷል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version