አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በአፍሪካ የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታን ለማሳደግ “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለልማት” የተሰኘ የ1 ቢሊየን ዶላር ኢኒቬቲቭ ይፋ አድርጋለች፡፡
ኢኒሼቲቩ በአፍሪካ የዲጂታል መሰረተ ልማትን በማጠናከር በአህጉሪቱ የኢኮኖሚ እድገትን እና ማህበራዊ ልማትን ለማሳለጥ ያለመ ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተመላክቷል፡፡
የአቡዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ ካሌድ ቢን መሃሙድ ቢን ዛይድ አልናህያን ኢኒሼቲቩን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት ÷ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በአፍሪካ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ ናት፡፡
መርሐ ግብሩን የአቡዳቢ ፈንድ አካል የሆነው አቡዳቢ ኤክስፖርትስ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የውጭ እርዳታ ኤጀምሲ በትብብር ይተገብሩታል፡፡
ይህም አቡዳቢ ታዳጊ ሀገራት አርቴፊቫል ኢንተለጀንስን የመሰሉ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አካታች የኢኮኖሚ እድገት እንዲያስመዘግቡ የምታደርገውን ጥረት የሚያሳይ ነው፡፡
በተለይም በአህጉሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ የልማት ተግዳሮቶችን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ ለመፍታት ያስችላል፡፡
በተለይም በትምህርት፣ ግብርና፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ መሰረተ ልማት እና ሌሎች ዘርፎች የሚገጥሙ ተግዳሮችን በመቅረፍ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንደሚያስችል ነው የተመላከተው፡፡
ንቅናቄው ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የዘርፉ ራዕይ ጋር የተጣጣመ ሲሆን÷ ከአፍሪካ ብሎም ከዓለም ሀገራት ጋር ያላትን የተሳለጠ ግንኙነት ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተጠቁሟል፡፡
በመላኩ ገድፍ

