አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ታሪካዊና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ወደሆነ ከፍታ ትሸጋገራለች አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የትግበራ ምዕራፍ ይፋዊ የማጠናቀቂያና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትግበራ ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ ባለፉት አምስት ዓመታት መጠነ ሰፊ ትሩፋቶችን አስገኝቷል፡፡
በተለይም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ውጥኖችን የሚያግዙና ልዩ ትኩረት የሚሹ ሦስት ጉዳዮች መለየታቸውን ገልጸው፥ እነዚህም በፋይናንስ፣ በሰው ሀብት ልማትና በፖሊሲ ትግበራዎች አቅምን ማሳደግ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሁሉን አቀፍና አካታች የዲጂታል አገልግሎቶች የሚቀርቡበትና የውስጥ ፈጠራ የሚበረታታበት ሲሆን፥ ይህም ሙሉ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ለማሳካት ከተለመዱ ተፈጥሯዊ አካሄዶች ባለፈ መፍጠን፣መዝለልና ፈጠራን ያማከሉ አካሄዶችን መከተል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት የተቀረጸው ዲጂታል ኢትዮጵያን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆኑን ገልጸው፥ ይህም የመንግሰትን ልዩ ትኩረት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላትና የማኅበረሰቡን ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በለይኩን ዓለም

