አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በተልዕኮው ልዩና ስትራቴጂያዊ የሆነ ኤሊት የፖሊስ ኃይል መገንባቱ የፀጥታ ሪፎርማችን ትልቅ ማሳያ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አካዳሚ በራሱ አቅም ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የኮማንዶ ፖሊስ አባላት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘቴና ይህንን ጀግና የፖሊስ ሠራዊት በመመልከቴ የተሰማኝ ደስታ ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
መንግሥታችን በፀጥታ ዘርፉ ባከናወነው መጠነ ሰፊ ሪፎርም የፌዴራል ፖሊስ ዛሬ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ጠንካራ ዘብ፣ በሙያው ብቁና በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ በሕዝብ ፍቅርና አመኔታ የተገነባ ፕሮፌሽናል ተቋም ሆኗል ነው ያሉት።
ይህ ኤሊት የፖሊስ ሠራዊት ማንኛውንም ውስብስብና አስቸጋሪ የጸጥታ ስጋቶችን በአጭር ጊዜና በከፍተኛ ብቃት የመቀልበስ ልዩ አቅም ያለው ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የኢሊት ፖሊስ ሰራዊቱ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሰላም የሚፈታተኑ የሽብርና የከባድ ወንጀል ሙከራዎችን በብቃት የመከላከልና መቆጣጠር ኃላፊነት ተጥሎበታል በማለት ገልፀዋል።
ሀገራችን በሁሉም መስክ ለምታስመዘግበው ድል ዋነኛው መሠረት ሰላምና ፀጥታ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሰላም ሲሉ ሕይወታቸውን እስከመገበር የደረሰ መስዋዕትነት ለከፈሉና ሀገርን ለማጽናት በቁርጠኝነት ለቆሙ የፖሊስ አባላቶቻችን ትልቅ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።
የእስካሁኑ ስኬት ይበልጥ ለሥራ የሚያተጋ መሆኑን ገልጸው፤ በመጪው ግንቦት የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነፃ ሆኖ እንዲከናወን፣ እንደ ኮፕ32 ያሉ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መድረኮች እንዲሁም ደማቅ የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የፌዴራል ፖሊስ የተጣለበትን ታሪካዊ አደራ በብቃት እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
የዛሬ ተመራቂ የኤሊት ፖሊስ ሠራዊት አባላት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሉዓላዊነት ምልክት ናችሁ ሲሉ ገልፀው፤ ሀገርንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከየትኛውም አደጋ የመከላከል ኃላፊነታችሁን በታማኝነት እንድትወጡ አደራ ማለት እፈልጋለሁ ብለዋል።

