Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከ33 ሺህ በላይ የፌደራል ግብር ከፋዮች በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ክፍያ ፈጽመዋል

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ33 ሺህ በላይ የፌደራል ግብር ከፋዮች በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴ አማካኝነት ክፍያ ፈጽመዋል አሉ የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ዳዊት ውብሸት፡፡

ሚኒስቴር ዴኤታው ዳታን መሰረት ያደረገ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት ለመገንባትና ዲጂታላይዜሽንን እውን ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ከ58 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች ኤሌክትሮኒክስ ዘዴን በመጠቀም ግብር ለመክፈል ያሳወቁ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ ከ33 ሺህ በላይ የሚሆኑት ክፍያ ፈጽመዋል ነው ያሉት፡፡

ከ2013 እስከ 2017 በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ክፍያ የፈጸሙት 6ሺህ 762 ግብር ከፋዮች መሆናቸውን አስታውሰው፥ በአሁኑ ሰዓት ወደ 33 ሺህ ከፍ ማለቱ ተጠቃሚው በስፋት ወደ ዲጂታል ስርዓቱ እየገባ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከል ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ግብር መሰብሰብ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም በ2013 ዓ.ም 279 ነጥብ 44 ቢሊየን ብር የነበረውን ገቢ በ2017 ከ900 ቢሊየን በላይ ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ሚኒስቴሩ በተያዘው አመት በትሪሊየን ለማሳካት ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ከመስራት በተጨማሪ የመሶብ አገልግሎትን በመጠቀም በቴክኖሎጂ የበለጸገ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ስርዓቱ ግብር ከመሰብሰቡ በፊት ሊገኝ የሚችለውን የገቢ መጠን ለማወቅ እንዳስቻለ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የታክስ ስርዓትን ወደ ታክስ አስተዳደር በመቀየር የነበሩ ክፍተቶችን በመቅረፍና የስራ ባህልን በማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ግብር ከፋዩ ከማንኛውም የሰው ንክኪ በጸዳ መንገድ በዲጂታል አማራጭ ያለበትን ግብር መክፈል የሚያስችለውን ስርዓት ለማስፋት ሚኒስቴሩ እየሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

በአቤል ነዋይ

Exit mobile version