Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጨረቃ ላይ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ የመገንባት ህልም

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያ መንግሥት የጠፈር መርሐ ግብሩ የኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ጨረቃ ላይ በ10 ዓመታት ውስጥ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ የመገንባት ዕቅድ አለው ተባለ።

ወደ ጠፈር በሚደረግ ጉዞ ግንባር ቀደም የነበረው የሩሲያ የህዋ ጉዞ ታሪክ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአሜሪካ እና ቻይና ብልጫ እየተወሰደበት ይገኛል።

አሁን ላይ ይህንን በሚቀይር መልኩ የሩሲያ መንግስት በፈረንጆቹ 2036 የጨረቃ ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ማቀዱን የሩሲያ የኒውክሌር ኩባንያ (ሮሳቶም) አስታውቋል።

ተቋሙ የኃይል ማመንጫው የኒውክሌር ማብላያ እንደሆነ ባይገለጽም ሮሳቶም እና የሩሲያ ግንባር ቀደም የኒውክሌር ምርምር ተቋም በፕሮጀክቱ ላይ እንደሚሳተፉ ጠቁሟል።

የኃይል ማመንጫው ዋነኛ ዓላማ ሩሲያ በጨረቃ ላይ ለሚከናወኑ የአሰሳ፣ ቅኝት እና የሩሲያ-ቻይና ዓለም አቀፍ የጨረቃ ምርምር ጣቢያ መሠረተ ልማት ፕሮግራሞች ኃይል ማቅረብ እንደሆነ አመላክቷል።

ፕሮጀክቱ ቋሚ የሆነ ለረጅም ጊዜ ተልዕኮዎች የሚያገለግል ሳይንሳዊ የጨረቃ ጣቢያ ለመፍጠር ወሳኝ እርምጃ እንደሆነም ተገልጿል።

የሮሳቶም ኃላፊ ዲሚትሪ ባካኖቭ ከወራት በፊት ከኮርፖሬሽኑ ዓላማዎች መካከል በጨረቃ ላይ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ መገንባት እና የምድር “እህት” በመባል የምትታወቀውን ፕላኔት ቬነስን ማሰስ እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ነገር ግን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫን በጨረቃ ላይ ለመገንባት አሜሪካም በዕቅዷ ውስጥ እንዳካተተችው እና በፈረንጆቹ 2030 በጨረቃ ላይ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ፍላጎት እንዳላት የሀገሪቱ ብሔራዊ የበረራ እና የጠፈር አስተዳደር (ናሳ) ከወራት በፊት መግለጹን የዘገበው ሮውይተርስ ነው።

ዓለም አቀፍ ህጎች የኒውክሌር ጦር መሳሪያን በህዋ ላይ ማስቀመጥን የሚከለክሉ ቢሆንም የኒውክሌር ኃይል ምንጮችን ወደ ህዋ ውስጥ ማስገባትን አያግድም።

በዮናስ ጌትነት

 

Exit mobile version