አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በዛሬው ዕለት አራት የምድብ ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
ምሽት 5 ሰዓት ላይ በምድብ ሶስት የተደለደሉት ናይጄሪያና ቱኒዚያ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ቡድኖቹ የምድብ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በድል መወጣታቸው ይታወሳል።
ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ምሽት 2:30 ላይ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸው ሽንፈት ያስተናገዱት ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ ይገናኛሉ።
በምድብ አራት የተደለደሉት ቤኒን እና ቦትስዋና ቀን 9:30 ሲገናኙ፤ ሴኔጋል እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አመሻሽ 12:00 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ትናንት በተካሄደ ጨዋታ ግብጽ ደቡብ አፍሪካን 1 ለ 0 ስታሸንፍ፤ አንጎላ እና ዚምባቡዌ 1 ለ 1፣ ዛምቢያ እና ኮሞሮስ 0 ለ 0 እንዲሁም አዘጋጇ ሀገር ሞሮኮ እና ማሊ 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት መለያየታቸው ይታወቃል።

