Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የክትባት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማጠናከር…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁሉን አቀፍ የክትባት አገልገሎት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል አለ የጤና ሚኒስቴር፡፡

በሚኒስቴሩ የክትባት አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ አቶ መልካሙ አያሌው እንዳሉት÷ ክትባት በሽታ የመከላከልና መቋቋም አቅም በማሳደግ ጤናማ እና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ያስችላል፡፡

በሽታዎችን መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ መሰረት ባደረገው የጤና ፖሊሲ የዜጎችን ጤና ይበልጥ ለመጠበቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የክትባት አገልግሎትን ለማስፋትና ለማጠናከር በተከናወነ ሥራ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው÷ በቀጣይ ውጤቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከባለድሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡

በተለይም የእናቶችና ሕጻናትን ጤና ለማሻሻል የክትባት ፕሮግራም ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑ ታምኖበት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ይሁን እንጂ የክትባት ተደራሽነት ውስንነት አሁንም እንደሚስተዋል ገልጸው÷ ችግሩ በተለይም ከማዕከል ርቀት ባላቸው አካባቢዎች ላይ በስፋት እንደሚከሰት አመልክተዋል፡፡

ይህም በአብዛኛው ከግንዛቤ ማነስ እንደሚፈጠር የተናገሩት ኃላፊው÷ ችግሩን ለመቀነስ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻዎች በትብብር እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር በመሰል አካባቢዎች ላይ የሕይወት አድን መድኃኒቶችንና ክትባቶችን በድሮን የማድረስ ሥራ በቅርቡ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

ለአብነትም ባለፈው እሑድ የማርበርግ ቫይረስ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሕይወት አድን መድኃኒቶችንና ክትባቶችን በድሮን አሰራጭቷል፡፡

ለዜጎች ጥራት ያለው ክትባት ተደራሽ በማድረግ በሽታ የመከላከል አቅምን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አቶ መልካሙ አረጋግጠዋል፡፡

ክትባት ላልጀመሩና ጀምረው ላቋረጡ ሕጻናት የማካካሻ ክትባት አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ አዳዲስ ክትባቶችን ወደ መደበኛ አገልግሎት በማስገባት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የማህጸን በር ካንሰር እና የጉበት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን ጨምሮ ሁሉንም መደበኛ ክትባቶች ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መገናኛ ብዙሃን የአንበሳውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሥራውን ለማሳለጥም በመደበኛ የክትባት አገልግሎት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version