Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዜጎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችል ተልዕኮዎች አሉት – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዜጎች በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችል ተልዕኮዎች አሉት አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

አገልግሎቱ ዲጂታል ሉዓላዊነቷን የጠበቀች፣ በፈጠራና ቴክኖሎጂ የላቀች፣ የበለፀገች ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ÷ መንግሥት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ወሳኝ ናቸው በማለት ከነደፋቸው ትልሞች መካከል ዲጂታል ኢትዮጵያን መገንባት ትልቅ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ ነው ብሏል፡፡

የኢትዮጵያን መፃዒ እድል በዛሬና በነገ ትውልድ ፈጠራና ቴክኖሎጂ እድገት ላይ ለመገንባት ያለመው ዲጂታል ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ጥራት ያለውና ከዘመኑ ጋር የሚጓዝ አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል ውጤት እየታየበት ይገኛል ሲልም ገልጿል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ዲጂታል ሉዓላዊነቷን የጠበቀች፣ በፈጠራና ቴክኖሎጂ የላቀች፣ የበለፀገች ኢትዮጵያ

መንግሥት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ወሳኝ ናቸው በማለት ከነደፋቸው ትልሞች መሐከል ዲጂታል ኢትዮጵያን መገንባት ትልቅ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያን መፃዒ እድል በዛሬና በነገ ትውልድ ፈጠራና ቴክኖሎጂ እድገት ላይ ለመገንባት ያለመው ዲጂታል ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ጥራት ያለው ከዘመኑ ጋር የሚጓዝ አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል ውጤት እየታየበት ይገኛል፡፡

እንደሚታወቀው ይህን ትልም ለማሳካት መንግሥት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ቀርፆ ወደ ስራ ገብቶ ነበር። በውጤቱም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በሁሉም መስኮች አስደናቂ ውጤት የተመዘገበበት ሲሆን ስትራቴጂው ስኬታማ ተልዕኮዎቹን አጠናቆ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አስረክቧል፡፡

በዲጂታል 2025 የቴሌኮምን ገበያ በመክፈትና በማስፋት የኢንተርኔት እና ሞባይል አገልግሎት ተደራሽነትን ማሳደግ እንዲቻል አድርጓል።

ደህንነቱ የተጠበቀ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (Fayda) ለመላው ኢትየጵያውያን ለማዳረስ የተከናወነው ፕሮጀክት ፣ የኢ-ገቨርናንስ አገልግሎቶች ፣የመሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት የዘመነ እና የተቀላጠፈ አገልግሎት በማዳረስ በኩል ትልቅ እመርታ የታየበት ስራ ነው፡፡

ሌላው የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ፕሮግራም የዲጂታል ክህሎትን በማስፋፋት በኩል አመርቂ ውጤት የታየበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መመስረት፣ የፐብሊክ ኢንፍራስትራክቸር (PKI) መጀመር፣ የኢንተርኔት ፋይበር እና 4G/5G ማስፋፋት፣ ዲጂታል ፋይናንስ ዲጂታል ግብይቶች የመሳሰሉት ሁሉ የዲጂታል 2025 ተልዕኮ ስኬታማነት ማሳያዎች ናቸው።

ይህንን መነሻ በማድረግ መንግሥት የዲጂታል 2030ን ስትራቴጂ በመቅረፅ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል፡፡ ይህ ስትራቴጂ ዲጂታል ሉዓላዊነቷን የጠበቀች፣ በፈጠራና ቴክኖሎጂ የተመሠረተች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚያግዝ ስትራቴጂ ሲሆን ስትራቴጂው ቴክኖሎጂን የኑሮ ዘይቤ በማድረግ ሁሉን አቀፍ ብልፅግናን ማረጋገጥ ዓላማው ያደረገ ነው፡፡

የስትራቴጂው ምሰሶዎች ተብለው ከተቀመጡት ውስጥ
1) ተደራሽነትን ማስፋት፡ በከተማና በገጠር መካከል ያለውን የዲጂታል ልዩነት በማጥበብ ዜጎች በየትኛውም ስፍራ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ።
2) እኩል ዕድሎችን መፍጠር፡ ዜጎች በዲጂታል ኢኮኖሚው ውስጥ እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታን ማመቻቸት።

3) መተማመንን መገንባት፡ በተቋማትና በዜጎች መካከል የሳይበር ደህንነትና የውሂብ (Data) ጥበቃን በማረጋገጥ ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ሥርዓት መገንባት ይገኙበታል፡፡

እንዲሁም ይህ ስትራቴጂ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ተወዳዳሪነት የምታረጋግጥበትና የመንግሥት አገልግሎቶች በግልጽነት ለዜጎች የሚቀርቡበትን መንገድ የሚያሳልጥ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ ስትራቴጂው በግብርናና በጤና፡ ዘመናዊ የዲጂታል መሣሪያዎችን በማካተት ምርታማነትንና የአገልግሎት ጥራትን ማሳደግ፣ በፋይናንስና በትምህርት፡ የፋይናንስ አካታችነትን ማረጋገጥና ለነገው ትውልድ የዲጂታል ፈጠራ አሳቢነትን ማሳረጽ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፡ ለዲጂታል ሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ምኅዳር በመፍጠር ወጣቶች የፈጠራ አቅማቸውን ወደ ኢኮኖሚ እሴት እንዲቀይሩ ማስቻል የመሳሰሉት ፋይዳዎች ይኖሩታል፡፡

የኢትዮጵያን የቱሪስት መስህቦች በዲጂታል አማራጭ ለዓለም በማስተዋወቅ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግም የዚህ ስትራቴጂ ሌላው ግብ ነው፡፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሀብት ፈጣሪ አምራች ስታርታፖችና የዲጂታል ክህሎት አቅም በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር ፣የፋይናንስ አካታችነትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማረጋገጥና ዜጎች በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ እንዲችሉ ማድረግ የሚያስችል ተልዕኮዎችም አሉት፡፡

Exit mobile version