Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የፍትሕ አገልግሎቱን የሚያሳልጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትግበራ የፍትሕ አገልግሎቱን ለማዘመን የተጀመሩ ተግባራትን ለማሳለጥ በትኩረት ይሰራል አሉ የፍትሕ ሚኒስትር ሀና አርዓያሥላሴ፡፡

ሚኒስትሯ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት፣ በታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ አቅርበዋል።

የሰዎችን ክብር የሚነኩ ንግግሮች፣ ቤት እንሰራላችኋለን በሚል የበርካታ ዜጎችን ሀብት ተቀብለው የሚሰወሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥርና የህግ እርምጃ የተመለከቱ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።

ሚኒስትሯ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፥ በማረሚያ ቤቶች በተከናወነ ጠንካራ ሪፎርም የታራሚዎችና ተጠርጣሪዎችን መብት መጠበቅ የሚያስችል መሰረተ ልማት በማሟላት ይነሱ የነበሩ ችግሮችን በመሰረታዊነት ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር ፈጣንና ቀልጣፋ የሕግ አገልግሎት ለመስጠት በክልሎች ቅርንጣፎችና ንዑስ ቅርንጫፎችን መክፈቱን ገልጸው፥ የተሳለጠ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡

በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ ዜጎች የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ባሉበት ሆነው መከታተል የሚችሉበትን ዕድል የማስፋት ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡

የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ህጉን ጨምሮ በፍትሕ ስርዓት ሪፎርሙ የወጡ በርካታ ህጎች በፍትሕ አሰጣጥ ስርዓቱ ላይ ለውጥ ማምጣታቸውን ተናግረዋል።

ከለውጡ ወዲህ አፋጣኝ ሕጎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር ተጣጥመው እንዲሻሻሉና በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ክትትልና ቁጥጥር መደረጉን አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሯ እንዳሉት ከክልል የፍትሕ ተቋማት ጋር በመተባበር የተሳለጠ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ሲሆን፥ በዚህም ከህግ ማውጣት እስከ ህግ ተገዥነት ትግበራ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

የወንጀል ምርመራና የክስ ሂደትን በሚፈለገው ፍጥነት ለማስኬድ የፖሊስ፣ አቃቤ ህግና ፍርድ ቤቶች ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።

የሀገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትህ የፖለቲካ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁነኛ መፍትሔዎች ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ዜጎችን ቤት እንሰራላችኋለን በማለት የሚያታልሉ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ለአብነትም በዚህ መንገድ ከህዝብ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ ያጭበረበሩ ግለሰቦች ላይ ክስ እንደተመሰረተ ጠቁመዋል፡፡

Exit mobile version