አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የመጪው ገና በዓል ግብይት የተረጋጋና በቂ የምርት አቅርቦት ያለበት እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አለ የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ፡፡
የቢሮው ሃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ÷ ለበዓሉ አስፈላጊ የፍጆታ እቃዎችን አቅርቦት ለማሳለጥ በምክትል ከንቲባው የሚመራ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡
በዚህም ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች በበቂ መጠን በገበያ ማዕከላት፣ በሰንበት ገበያዎች እንዲሁም ለገና በዓል በተዘጋጁ ባዛሮች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ተፈላጊነታቸው የሚጨምሩ ምርቶች ላይ የተለየ ትኩረት በመስጠት የማሕበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ለበዓሉ 279 ሺህ 620 የዳልጋ ከብት፣ 294 ሺህ 620 በግና ፍየል በመዲናዋ በአምስቱም በሮች በሚገኙ የቁም እንስሳት የገበያ ማዕከላት እየቀረቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም 633 ሺህ 400 ዶሮ እና 15 ሚሊየን እንቁላል በሰንበት ገበያዎችና ለገና በዓል በተዘጋጁ ባዛሮች እየቀረቡ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
9 ሺህ 294 ኩንታል የሰብል ምርቶች እና 416 ሺህ 205 ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶች ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እየሆኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በበዓል ግብይት ወቅት የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ የንግድ ተግባራትን ለመከላከል ከከተማ እስከ ወረዳ የተዋቀረው ግብረ-ኃይል እና የቴክኒክ ኮሚቴ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የምግብ ፍጆታ ምርቶች በሕገ ወጥ መንገድ እንዳይከማቹና ሰው ሰራሽ እጥረት እንዳይፈጠር የመጋዘኖች ፍተሻ በማካሄድ የሚገኙ ጥፋቶች ላይ የእርምት ርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት፡፡
የእህል፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቁም እንስሳት የገበያ ማዕከላት ላይ የዋጋ ቁጥጥር እና የደረሰኝ ግብይት እንዲከናወን እንደሚደረግ ጠቁመው÷ በስጋ ቤቶችና ሌሎች ሱቆች ላይ የሚዛንና መስፈሪያ መሳሪያዎች ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

