Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ላይ አይተኬ ሚና አላቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት በሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አይተኬ ሚና እንዳላቸው በጽኑ በማመን ለተግባራዊነቱ እየሰራ ይገኛል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ “የምሁራን ሚና ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ምሁራን በሁለንተናዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሚና በሚመለከት ሰፊ ውይይት አድርገናል ብለዋል፡፡

ሀሳብ የለውጥ ኃይል ነው፥ምሁራን ደግሞ የለውጥ ወኪሎች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ምሁራን በማኀበረሰብ ውስጥ የሚፈጥሩት ለውጥ ሀገርን ወደ ብልጽግና እንደሚወስድ አመላክተዋል፡፡

ምሁራን ሀሳብ አክባሪና አፍቃሪ፣ ጥልቅ አሰላሳይ፣ አንባቢ፣ ችግር ፈቺና መፍትሄ አሳሽ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የመደመር መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ላይ አይተኬ ሚና እንዳላቸው በጽኑ እንደሚያምን ገልጸው፥ ለተግባራዊነቱም እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ተቋማቱ የመማር ማስተማር እንዲሁም የምርምር ስራዎችን ከቴክኖሎጂ ጋር በማናበብ ወደ ፈጠራና ተግባር መለወጥ ይጠበቅባቸዋል ያሉ ሲሆን፥ ይህም የኢትዮጵያን ብልጽግና በተደመረ አቅም ለማፋጠን ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል።

Exit mobile version