Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጤና ቁጥጥር ሥርዓት ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጤና የቁጥጥር ሥርዓት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ለመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
መርሐ ግብሩ “ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ለማይበገር የጤና ሥርዓት” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዴዔታዎችና የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ከ1 ሺህ 200 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
ጤና ሚኒስቴር ለጤና ቁጥጥር አፈጻጸም የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና እቅዶችን በማዘጋጀት የሕብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ተመላክቷል።
የሕክምና ግብዓቶች ተደራሽነት፣ ፍትሃዊነት፣ ጥራትና ደህንነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የአካባቢ ጤና አጠባበቅና የጤና ባለሞያዎችን አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

 

የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ፍሬሕይወት አበበ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ በመከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ትኩረት ያደረገው የጤና ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓትን ማረጋገጥ ይገባል።

በሀገሪቱ ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ሥርዓት እንዲኖር የቁጥጥር ተቋማት በሰው ኃይል፣ በአሰራር፣ በቴክኖሎጂና በግብዓት ያላቸውን አቅም ማጎልበትና የተጠሪ ተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም በመድኃኒት አቅርቦት ደህንነት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታዋ ፥ በዚህ ረገድ የመድኃኒት አቅርቦትን በዲጂታል ሥርዓት ለማስተሳሰር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

 

በኃይለማርያም ተገኝ
Exit mobile version