Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አየር መንገዳችን የአፍሪካ አስተሣሣሪነቱን የሚያጸና አዲስ ምዕራፍ ጀምሯል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ጥር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አየር መንገዳችን ለ80 ዓመታት የዘለቀውን የአፍሪካ አስተሣሣሪነቱን የሚያጸና አዲስ ምዕራፍ ጀምሯል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ፥ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በጉባ ካበሠሯቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውንና በአፍሪካ ግዙፉን የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ዛሬ በቢሾፍቱ አስጀምረናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከስምንት አስርት ዓመታት በፊት በጥቂት አውሮፕላኖች ጉዞውን ጀመረ፤ ዓላማው ኢትዮጵያን ከዓለም ጋር ማገናኘት ብቻ አልነበረም፤ የአፍሪካን ክብር በሰማይ ላይ ከፍ አድርጎ ማሳየት ጭምር እንጂ ሲሉም አብራርተዋል።

በዓመት እስከ 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ ዐቅም የሚፈጥረው አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ የኩራት ታሪካችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የኢትዮጵያ ግልጽ ራዕይና የብልጽግና ጉዞ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የመንግሥታችንን በትልቁ አስቦ በትልቁ የማሳካት ዕይታን የሚገልጥ፣ የአፍሪካን የልዕልና ጉዞ በማረጋገጥ በዓለም አቪዬሽን መሪ ሚና እንዲኖራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የአየር መንገዳችንን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ይበልጥ ከፍ የሚያደርገው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳው የላቀ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አየር መንገዱ ወደ አፍሪካ መግቢያ እና መውጫ ዋናው በር ሆኖ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ የፈጠራና ፍጥነት ጉዟችን በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።

Exit mobile version