አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደኅንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ተቋም ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ዛሬ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።
አየር መንገዱ ሰላማዊና ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው ሊባል የሚያስችል ውጤቶች ባለፉት 10 ዓመታት ማሳየት መቻሉን ተናግረዋል።
በፈጠራና በትጋት የሚሰሩና ራሳቸውን ከዓለም የአመራር ብቃት ጋር የሚያስተካክሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ባለፉት አስርት ዓመታት አየር መንገዱን መምራት መቻላቸውን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ወታደሮች ተለይተው አይታዩም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በየቀኑ የተሸከሙትን ሰንደቅ ዓለማ አክብረው ለሁሉም ዜጋ ኩራት ለመሆን በከፍተኛ ትጋት ያገለገሉ የሀገር ኩራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 26 ሺህ የሚጠጋ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች እንዳሉት ጠቁመዋል።
ተቋሙ ሁሌም ተማሪ ነው፤ አዲስ አውሮፕላን አዲስ ቴክኖሎጂ፣ አዲስ ዕውቀት ዓለም ላይ ተፈጠረ ሲባል ያንን ዕውቀት ለመገብየት አውሮፕላኑንም ለአፍሪካ ለማስተዋወቅ ከማንም ቀድሞ የሚገኝ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በጥገናና በትምህርት ዘርፍ ያስገኘው እመርታ አስደናቂ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመለዋወጫ እቃዎችን ለማምረት ስራዎች መጀመሩን ተናግረዋል።
በአድማሱ አራጋው

