አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለት አንጓ የተከፈለ ነገን መዋጀት የሚያስችል ስራዎች ጀምሯል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ማስጀመሪያ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ አየር መንገዱ የተሳካ 80 ዓመታት ተጉዟል፤ የሚቀጥለው 80 ዓመት ከባለፈው በብዙ መልኩ ይለያል።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የማንዘጋጅ ከሆነ አብዛኛውን የአውሮፕላን ተግባራት የሚፈጽመው ማሽን በሚሆንበት ሰዓት ይህንን ክብራችንን ይዘን መቀጠል አንችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለት አንጓ የተከፈለ ነገን መዋጀት የሚያስችል ስራዎችን ጀምሯል ብለዋል።
የመጀመሪያው የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ወይም ህፃናት ላይ አበክሮ መስራት መሆኑን ጠቅሰው÷ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ35 ሺህ በላይ መዋለ ሕፃናት በሀገር ደረጃ ገንብተናል ነው ያሉት።
ባለፉት ስድስት ዓመታት ታዳጊዎች በሰውነታቸው የበረቱና ከጓደኞቻቸው ጋር የሚውሉ እንዲሆኑ በርካታ አረንጓዴ ስፍራዎችን ገንብተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በአዲስ አበባ ብቻ ልጆች የሚውሉበት ከ1 ሺህ 600 በላይ ትናንሽ ስታዲየሞች መገንባታቸውን ገልጸዋል።
በመቀጠልም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በዓለም ሁለተኛ የሆነውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ እናስጀምራለን ብለዋል።
ታች ላይ እና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚሰራው ስራ ሲደመር የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚቀጥለውን 80 ዓመት የሚገጥመውን አዳዲስ ዕውቀትና ፈተና ተጋፍጦ ለማለፍና ለመሻገር የሚያስችለውን ብቃት እንዲጎናጸፍ እንደሚያደርገው አብራርተዋል።
ዛሬ በሰማይ ላይ ለሚበሩ መርከቦች 130 ሚሊየን ሕዝብ የሚመጥን ወደብ በዚህ ስፍራ ስራ አስጀምረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረን በአጠቃላይ ብቃቱ ይለያል ሲሉም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ 700 ሄክታር አካባቢ የመሬት ስፋት እንዳለው ገልጸው÷ ዛሬ ግንባታ የተጀመረው የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ 3 ሺህ 900 ሄክታር ገደማ የአየር መንገዱ ብቻ እንዲሁም ለተነሱ ሰዎች የተጠቀምናቸውን ቦታዎች ሲጨምር 5 ሺህ ሄክታር የአየር መንገዱን ከባቢ የሚሸፍን ስፋት ያለው ቦታ ነው ብለዋል።
ይህም ስፋት በዚያው ልክ በአየር ላይ የሚመላለሱ መርከቦችን በብቃት ማስተናገድ ችሎ የኢትዮጵያን የዕድገት ስብራት የሆነውን ሎጂስቲክስ ለመፍታት በእጅጉ ስለሚያግዝ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
በአድማሱ አራጋው

