አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እያንዳንዱ የሚወረወሩብንን ድንጋዮች ለግንባታ እንደሚውል ብሎኬት እንጠቀማቸዋለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በትናንትናው ዕለት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው፡፡
በመልዕክታቸውም÷ እያንዳንዱን ጦር እና ፍላፃ እንደ አርማታ እንዲሁም እያንዳንዱን ስድብ እና የቅናት ጩኸት እንደ ማንቂያ ደወል እንጠቀምበታለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በድምሩ ግን የኢትዮጵያን ብልፅግና እና የኢትዮጵያን መፅናት ማረጋገጥ የሆነውን ታላቁ ህልማችንን በፈተናዎች ውስጥ ሆነን እናሳካለን ነው ያሉት፡፡
“ከሚያድግ ልጅ ጋር አትቀያየም” የሚለውን ሀገርኛ አባባል የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በቅርብና በሩቅ ያሉ ሀገራት ከሚያድግ ሀገር ጋር እንዳይቀያየሙ መክረዋል።
ይህ የሚያድግ ሀገር ከወዲሁ እያደገ ያለ፣ ለማደግ ህልም ያለው፣ የጠራ ሀሳብ ያለው፣ ሀሳቡም በተግባር የታየ መሆኑን በመጥቀስ፤ ነገ የሚታደጋቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሀገራት ከሚያድግ ሀገር ጋር ላለመቀያየም ራሳችሁን ምከሩ፣ ገስጹ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

