Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ውጤታማነትና ተጠያቂነትን መሰረት ያደረጉ የጤና ልማት ስራዎች…

‎አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውጤታማነትና ተጠያቂነትን መሰረት ያደረጉ የጤና ልማት ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው አለ የክልሉ ጤና ቢሮ።
‎
ቢሮው በክልሉ የጤና አገልግሎትን በመሰረታዊነት ማሻገር የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና “ጠንካራ የአመራር ግንባታ ለውጤታማ የጤና ስርዓት” በሚል መሪ ሐሳብ ለዘርፉ አመራሮች እየሰጠ ይገኛል።
‎‎
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ውጤታማነትንና ተጠያቂነትን መሰረት ያደረጉ የጤና ልማት ስራዎች በክልሉ ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው።
‎‎
‎የአቅም ግንባታ ስልጠናው የተጠናከረ የጤና ሥርዓት መፍጠር ላይ ያተኮረ መሆኑን አንስተው÷ ባለቤትነትን መፍጠርና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
‎
‎በክልሉ የጤናውን ዘርፍ ለማሻገር ተግዳሮት የሆኑ 15 ጉዳዮች በሳይንሳዊ ጥናት መለየታቸውን ጠቅሰው÷ ለዚህም 12 ስትራቴጂካዊ መፍትሄዎች በጥናቱ መቅረባቸውን ጠቁመዋል።
‎
‎ስልጠናውም ከተደረገው ሳይንሳዊ ጥናት መነሻ መዘጋጀቱን አመላክተዋል።

‎በክልሉ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ በርካታ የጤና ልማት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙና የጤና ተቋማትን ዲጂታላይዝ በማድረግ አገልግሎቶቹ ከወረቀት ነጻ ለማድረግ የሚያስችሉ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
‎
‎ከዛሬ ጀምሮ ለስምንት ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ከክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮች መሳተፋቸውን የቢሮ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል።

Exit mobile version