Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል አሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ አቶ አደም ፋራህ÷ እንደ ገዥ ፓርቲ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን እና ያለፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በሁሉም የምርጫ ክልሎች ያለው የሰላም ሁኔታ ተገምግሞ ምርጫ ለማከናወን የሚያስችሉ የሰላምና ፀጥታ ስራዎች እየተሰሩ ነው በማለት ገልጸው÷ ፓርቲው በምርጫው በብቃት ለመሳተፍ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወኑ የፓርቲ ስራዎች በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን እና ተሞክሮ የተወሰደባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የልማት ስራዎችን የህዝብን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መንገድ በመምራት  ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የተደረጉ ጥረቶች ተስፋ ሰጪ ውጤት እንዳስመዘገቡ ተናግረዋል።

የፓርቲው ኢኒሼቲቮችና ሰው ተኮር ስራዎች አፈጻጸም የተሻለ ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸው፣ በዚህም በየአካባቢው ያሉ እምቅ አቅሞችን ለይቶ በመጠቀም ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ስኬቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ትርክት እንዲጎለብት በማድረግ ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር መደረጉን መግለጻቸውን የፓርቲው መረጃ አመልክቷል።

የፓርቲ ዕሳቤዎችን በአግባቡ የተረዳ አመራር ለመፍጠር በተደረገ ጥረት የአመራር ብቃትን ማሳደግ እና የፓርቲ አደረጃጀትና አሰራርን ማጠናከር ተችሏል ብለዋል።

የትርክት የበላይነት ለማስረፅ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን የተሰሩ ተግባራት በርካታ ስኬቶችን በማስመዝገብ የህዝብ ቅቡልነትን ማሳደግ መቻሉን አስገንዝበዋል።

Exit mobile version