አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባስኬት ብሔረሰብ የምስጋና በዓል ‘ሾልኣ-ካሻ’ በላስካ ከተማ በአደባባይ እየተከበረ ነው።
“ባህላዊ እሴቶቻችን ለትውልድ ግንባታና ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ በሚገኘው ዓመታዊ የምስጋና በዓል ‘ሾልኣ-ካሻ’ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የባስኬቶ ዞን ነዋሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
‘ሾልኣ-ካሻ’ የልዩነት አጥሮችን በማፍረስና ግላዊ እይታዎችን በማምከን ለጋራ ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጥበት የምስጋና በዓል መሆኑ ተገልጿል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ደሳለኝ እንዳሉት፤ የአንድነት፣ የህብረትና የምስጋና በዓል የሆነው ‘ሾልኣ-ካሻ’ በዓል ሀገራዊ አንድነትንና አብሮነትን ለማጽናት የጎላ ሚና ይጫወታል።
የባስኬት ብሔረሰብን ባህልና ወግ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ‘ሾልኣ-ካሻ’ የብሔረሰቡን ባህልና ወግ ለማስተዋወቅ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉ ፓናል ውይይትን ጨምሮ በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር መቆየቱን ለፋና ዲጂታል የገለጹት ደግሞ የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ኃይለኢየሱስ አባይነህ ናቸው።
የባስኬት ብሔረሰብ በየዓመቱ የምርት መድረስና መሰብሰብን ተከትሎ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት ‘ሾልኣ-ካሻ’ ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲተላለፍ ምሁራን እና የአከባቢው ነዋሪዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

