አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘርፍ እና በማክሮ ደረጃም የመጡት አጠቃላይ ለውጦች እያንዳንዱ ዜጋ በቅርብ ርቀት የሚመለከተው ውጤት እያመጡ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁልፍ የመንግሥት ፋይናንስና ሌሎች የዘርፉ ተቋማትን ያሰባሰበው ‘የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ’ ኮንፈረንስ ላይ የእሳት ዳር ወግ ቆይታ እንዳሉት፤ ስብራት የገጠመውን የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ ለመቀየር ሪፎርም ሲጀመር ጉዳዩ ከበርካታ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነበር።
በማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የፋይናንስ ዘርፉ እንደነበረ ተናግረዋል።
በዘርፉ ውስጥ ጥራት ያለው አገልግሎት አለመኖር፣ የፋይናንስ ፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠን፣ ሀገራዊ ዕዳ እና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች በዘርፉ ጎልተው የሚታዩ ችግሮች እንደነበሩ አውስተዋል።
በዚህም እያንዳንዱ ችግር በማክሮ ደረጃ ታይቶ ካልተፈታ ኢኮኖሚውን የሚያናጋ ችግር ሲፈጠር ያንን ተቋቁሞ ሀገር እና ሕዝብን ማሻገር እንደማይቻለው ጠቅሰዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚውን ስብራት ከማስተካከል አንጻር ከፍተኛ ድርሻ ስላለው የተለየ ግምት ሰጥተን ሰርተናል ብለዋል።
የሪፎርም ሂደቱ ፈተና ብቁ ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ ማድረጉን አንስተው፤ ሪፎርሙን ስንጀምር የነበሩ ባለሙያዎች ከነበራቸው ዕውቀት አድገዋል፣ አዲስ የመጡት ደግሞ ኢትዮጵያ ተስፋ እንዳላት የሚያመላክቱ ሆነዋል ብለዋል።
የህዝብ ፋይናንስ አስተዳደር ስትራቴጂው የሚፈጠረው ማንኛውም ሀብት ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና ተገማችነት ባለው መንገድ ስራ ላይ ውሎ ዜጋው በሚነገር ጥቅል እድገት ብቻ ሳይሆን በቅርብ ርቀት እንዲሰማው ማድረግ ማስቻል መሆኑን አብራርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ እያንዳንዱ ሀብት ቴክኖሎጂን የሚጠቀም፣ በሕገ ወጥነት ማስቀረት እና ተጨማሪ ሀብት ለማምጣት ሪፎርሞችን በመስራት ሀብትን በማበራከት በሰው ሕይወት ላይ የሚጨበጥ ለውጥ እንዲያመጡ ማድረግ እንደሆነም አብራርተዋል።
በዚህም በሁሉም በዘርፍ እና በማክሮ ደረጃም የመጡት አጠቃላይ ለውጦች እያንዳንዱ ዜጋ በቅርብ ርቀት የሚመለከተው ውጤት እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በዮናስ ጌትነት

