Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የታክስ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያው በገቢ አሰባሰብ ሒደት ላይ ግልጽነት እንዲጎለብት አስችሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ ተግባራዊ የተደረገው የታክስ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ የገቢ አሰባሰብ ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲጎለብት አስችሏል አሉ፡፡
የአፍሪካ ከተሞች፣ ከንቲባዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙበት የልምድ ለውውጥ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በተካሄደው የ6 አፍሪካ ከተሞች የፋይናንስ አስተዳደር አፈጻጸም የዳሰሳ ጥናት አዲስ አበባ ከተማ የተሻለ ውጤት አስመዝግባለች።
በጥናቱ ላይ አዲስ አበባ፣ ናይሮቢ፣ ዳሬሰላም፣ ሉስካ፣ ኪጋሊ እና ያውንዴ የተሳተፉ ሲሆን ፥ አዲስ አበባ ከስድስቱ ዋና ዋና አመላካቾች ውስጥ በአምስቱ የተሻለ የገቢና የፋይናንስ ሃብት አስተዳደርን ማሳካት የቻለች ከተማ ሆናለች።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የገቢ አሰባሰብን በማጠናከር ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል፡፡
ይህም ሌሎች የአፍሪካ ከተሞች በዲጂታል ማሻሻያና በአዳዲስ ፈጠራዎች የፋይናንስ ምህዳሩን ማስፋት እንደሚችሉ ያመላከተ ነው ብለዋል።
መዲናዋ እንደ ሁሉም የአፍሪካ ከተሞች የሚያጋጥሟትን ፈጣን የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ ከፍተኛ የአገልግሎት ፍላጎትና ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የከተሞች ትራንስፎርሜሽን ከጠንካራ የመድብለ የፋይናንስ ሥርዓትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ውጪ ስኬታማ እንደማይሆን በመረዳት ባለፉት ዓመታት ጠንካራ ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት፡፡
አዲስ አበባ የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን ለመቀየር የሪፎርም ሥራዎችን እየሠራች እንደምትገኝ ነው ከንቲባዋ የገለጹት፡፡
ይህም የግብር አወሳሰንን ለማዘመን፣ የንግድ ፈቃድ አሰጣጥን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ለማጠናከር፣ የግብር ከፋዮች ምዝገባን ለማሻሻልና በገቢ አሰባሰብ ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነትን እንዲጎለብት ማስቻሉን አስገንዝበዋል።
ውጤቱ የተገኘው በጠንካራ የፖለቲካ አመራር፣ የቴክኒክ አቅም፣ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔዎችን በመስጠት እንዲሁም በመንግሥትና በዜጎች መካከል መተማመንን በማሳደግ እንደሆነም አመልክተዋል።
በአንዷለም ተስፋዬ
Exit mobile version