አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቤላሩስ በወታደራዊ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) እና የቤላሩስ መከላከያ ሚኒስትር ዲምትሪ ፓንተስ ተፈራርመዋል።
አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ስምምነቱ የኢትዮጵያን ወታደራዊ ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ለማሳደግና በወታደራዊ ምርቶች ራስን ለመቻል እየተደረገ ላለው ጥረት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል በመሆኗ የጋራ ገበያ እና ተጠቃሚነትን መፍጠር እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የተፈራረሙትን ስትራቴጂካዊ ስምምነት ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው ÷ ሀገራቱ የነበራቸውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነትን የሚያጠናክር እንደሆነም ተናግረዋል።
የሁለትዮሽ ስምምነቱ የሁለቱን ወዳጅ ሀገራት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ዲምትሪ ፓንተስ በበኩላቸው÷ ሁለቱ ወዳጅ ሀገራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው÷ ስምምነቱ በተለያዩ አዳዲስ ዘርፎች ለመሰማራት የሚያስችል ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የቤላሩስ አየር ሀይል ከነገ ጀምሮ በሚከበረው 90ኛው የኢትዮጵያ የአየር ሀይል የምስረታ በዓል ላይ የአየር ትርዒት እንደሚያቀርቡና ልዑካኑም እንደሚታደሙ የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

