Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ለዘላቂና ሁሉን አቀፍ እድገት ስትራቴጂያዊ አጋር መሆኗን ያሳየችበት ፎረም…

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ እያደረገች ያለው ተሳትፎ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ እድገትን ለማስቀጠል ስትራቴጂያዊ አጋር ሆና እንደምትቀጥል ቁርጠኝነቷን ያሳየችበት ነው፡፡
በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ተሳትፎውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ሚኒስትሩ በመጪው ጊዜ የዓለም የጤና ሥርዓትና ዘርፉን በፋይናንስ መደገፍ ላይ ትኩረቱን አድርጎ በተካሄደው መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ተሞክሮ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም በገጠር የሀገሪቱ አካባቢዎች የጤና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማሳደግ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና መሰል ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ያከናወነቻቸውን ተግባራት አብራርተዋል፡፡
የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል፣ ለክህሎት ልማት እንዲሁም የዲጂታል መሰረተ ልማት አቅርቦት የረጅም ጊዜ አጋርነትን ማጠናከርና ዘርፉን በዘላቂነት በገንዘብ መደገፍ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ባተኮረ መድረክ ላይ ሀሳባቸውን ያጋሩት ሚኒስትሩ ፥ ልዩ ልዩ ተጽዕኖዎችን የሚቋቋም ኢኮኖሚን ለመገንባት ወሳኝ ያሏቸውን አራት ተግባራት አመላክተዋል፡፡
እነዚህም ዘላቂ የፋይናንስ ሥርዓት፣ ቀጣናዊ የኃይል አቅርቦት መሰረተ ልማት፣ መሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎትን ለማስቀጠል የሚያስችሉ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች እንዲሁም የሰው ሀብት ልማትና ብዝሃ ኢኮኖሚን ማጠናከር መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የመንግሥትን የመፈጸም አቅም በማሻሻልና በሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም በዲጂታል ዘርፉ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡
እነዚህን ሥራዎች ኢትዮጵያ ለመጪው ጊዜ የዲጂታል ዓለም የተዘጋጀችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያስችሏታል ነው ያሉት፡፡
አቶ አሕመድ ሺዴ ከፎረሙ ጎን ለጎን ከቢል ጌትስ እንዲሁም ከአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ኮሚሽነርና ሌሎች የሀገራትና የተቋማት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡
በውይይቶቹም ኢትዮጵያ ኢኖቬሽንን ለማሳደግ፣ አጋርነትን ለማጠናከር እና ለዘላቂ ልማት ቁርጠኛ መሆኗን እንዳረጋገጠች ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ
Exit mobile version