አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆአን ዋድፉል ጋር ተወያይተዋል፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እንዳሉት ÷ ኢትዮጵያ እና ጀርመን ያላቸው ሁለንተናዊ ትብብር 120 ዓመታትን እንዳስቆጠረ አስታውሰዋል፡፡
በውይይታቸው በሀገራቱ መካከል የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ጉዳዮች ላይ በዝርዝር መምከራቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባዔ ጎን ለጎን ከጀርመኑ መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ ሜርዝ ጋር ያደረጉት ውይይት ለላቀ አጋርነት አዲስ መነቃቃት ፈጥሯል ነው ያሉት።
የዛሬው ውይይት የዚሁ ሒደት አንድ አካል መሆኑን ጠቁመው÷ በሀገራቱ መካከል ያለውን የፖለቲካ ፣ ኢኮኖሚና የልማት ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መግባባት ላይ መደረሱን አብራርተዋል።
ለግብርና፣ ለትምህርት፣ ለሥራ ስምሪት፣ ለሙያ ሥልጠና እና ለተፈጥሮ ሀብት ዘርፎች ቅድሚያ ለመስጠት መስማማታቸውን አመልክተዋል፡፡
በአየር ንብረት፣ በደኅንነት፣ ሽብርተኝነትን በመከላከልና የባለብዙ ወገን ትብብርን በማጠናከር ረገድ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቅሰዋል፡፡
ጆአን ዋድፉል በበኩላቸው የኢትዮጵያና ጀርመን ወዳጅነት ዘመናትን እንዳስቆጠረ አውስተው÷ የሀገራቱን ሁለንተናዊ ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው አግባቦች ላይ ከስምምነት መደረሱን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እያደረገች ያለው አስተዋጽኦ የሚደነቅ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
በወንድሙ አዱኛ

