Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ ተኝተን አናድርም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ ተኝተን አናድርም አሉ፡፡

የኢፌዲሪ አየር ኃይልን 90ኛ ዓመት በማስመልከት የተዘጋጀው የጥቁር አንበሳ የአየር ላይ ትርዒት በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባተላለፉት መልዕክት፥ የኢፌዲሪ አየር ኃይል ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም በሰው ኃይል ግንባታ ላይ እያከናወናቸው የሚገኙት ተግባራት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል

ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ብልፅግናን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በአፍሪካ ግንባር ቀደሙ የልማት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ባለፈው ዓመት 9 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን አውስተው፥ በዚህ ዓመት ቢያንስ 10 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ ያለፉት 6 ወራት የስራ አፈጻጸም አመላካች ነው ብለዋል፡፡

በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በኢኮኖሚና በማዕድን የምንሰራው ስራ በጠንካራ የጸጥታ ኃይል ካልተገነባ ዋጋ አይኖረውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይሄንን ጉዳይ በሚዛን አስተካክሎ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በወታደራዊ አቅማችንን ማሳደግ ስንችል የተፈራችና የተከበረች ሀገር ለልጆቻችን ማስረከብ እንችላለን ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በርከት ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመታጠቅ መሰራቱን ገልጸው፥ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አሁን ያለንበትን የአየር ኃይል አቅም በእጥፍ ለማሳደግ እንሰራለን ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ ተኝተን አናድርም ነው ያሉት፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version