አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አየር ኃይላችን በብዙ ከፍታዎች ውስጥ በማለፍ ለሀገር ኩራትና መከታ ሆኖ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሞከሩ ኃይሎችን ማሳፈር የቻለ ታላቅ ተቋም ነው አሉ፡፡
የኢፌዲሪ አየር ኃይልን 90ኛ ዓመት በማስመልከት የተዘጋጀው የጥቁር አንበሳ የአየር ላይ ትርዒት በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ላለፉት ዘጠኝ አስርት ዓመታት በብዙ ከፍታና ዝቅታ ውስጥ አልፏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በከፍታ ባሳለፋቸው ዓመታት ኢትዮጵያን ለደፈሩ አካላት ሁነኛ መድኃኒት ሆኖ መዝለቁን አውስተዋል፡፡
ከሁሉም አቅጣጫ ለሀገር ኩራትና መከታ በመሆን ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሞከሩ ኃይሎችን ማሳፈር የቻለ ታላቅ ተቋም መሆኑን አስታውሰው፥ ከኢትዮጵያ አልፎ ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ሰላም የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት፡፡
ለአብነትም የቅኝ ግዛት ዘመን እየተንኮታኮተ በነበረበት ወቅት የታንዛኒያን የአየር ክልል ከፖርቹጋል ቅኝ ገዥ ኃይሎች የተከላከለ አየር ኃይል እንደነበር አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ሰላም አስከባሪ ኃይል በማሰማራት አጋርነቷን በተግባር ባሳየችባቸው ዓመታት ከእግረኛ ጦሯ በተጨማሪ አየር ኃይላችን ለአፍሪካ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ስመጥር ተቋም ነው ብለዋል፡፡
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ከፍ ያለ ብቃትና ቁመና ላይ መሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህም በየዘመናቱ የነበሩ መንግስታት የሰሩት ስራ ድምር ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

