አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የማንንም አትፈልግም፥ የራሷንም አሳልፋ አትሰጥም፥ የሄደም ካለ ማወራረዷን አትተውም አሉ፡፡
የኢፌዲሪ አየር ኃይልን 90ኛ ዓመት በማስመልከት “የአንበሶቹ ሰማይ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የጥቁር አንበሳ የአየር ላይ ትርዒት በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተመልሶ የማደግና የትንሳዔ ምልክት የምትሆን ሀገር ናት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ትናንት ላይ የቆመች ሳትሆን ነገን ለመዋጀት አበክራ የምትሰራ ሀገር መሆኗን አውስተው፥ ሰላሟ፣ አንድነቷ እና ብልጽግናዋ በዜጎቿ የጋራ ትብብር እንደሚረጋገጥ አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የማንንም አትፈልግም፥ የራሷንም በየዋህነትና በተላላነት ለማንም አሳልፋ አትሰጥም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የተሰጠ ካለም ማወራረዷን እንደማትተው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ጥቅማቸውን ለሌሎች አሳልፈው እንደማይሰጡ የገለጹ ሲሆን፥ አየር ኃይላችን ይህን ፍላጎታችንን ለማሳካት ሁነኛ ተቋም ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የተጀመረውን ዕድገት ምንም አይነት እንቅፋት ሊያስቆመው እንደማይችል ገልጸው፥ ብልጽግናችንን በማረጋገጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ተረጂነትን ታሪክ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማረጋገጥ ስራ ከፊታችን ያለ ዐቢይ ተግባር መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህንን በመገንዘብ ሁሌም ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

