አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቅርቡ የማርበርግ ቫይረስ ስርጭትን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻሏ ትልቅ ስኬት ነው አሉ የሮተሪ ኢንተርናሽናል ፕሬዚዳንት ፍራንሲስኮ ኦሬዞ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጋር ባደረጉት ውይይት ጤና ሚኒስቴር በቅርቡ የማርበርግ ቫይረስ ስርጭትን ሙሉ ለሙሉ የተቆጣጠረበት መንገድ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ተናግረዋል።
ሮተሪ ኢንተርናሸናል ፖልዮን የማጥፋት ዘመቻ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ በመበጀት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ደግሞ ከ33 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ 99 ነጥብ 9 በመቶ ፖልዮ ከዓለም እንዲጠፋ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሮተሪ ኢንተርናሽናል ፕሬዚዳንቱ ጤና ሚኒስቴር የማርበርግ ቫይረስ ስርጭትን ሙሉ ለሙሉ የተቀጣጠረበትን መንገድ በማድነቅ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው ሮተሪ በፖሊዮ ማጥፋት ዘመቻና በጤና ጉዳዮች ላይ ለሚሰራቸው ስራዎች ምስጋና አቅርበው÷ ግንኙነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡ መሆናቸውን የሮተሪ ምዕራብ አዲስ አበባ ፕሬዚዳንት አቤኔዘር ፈለቀ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

