Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያና አሜሪካ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና አሜሪካ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) ከአሜሪካው የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አርኤም አንደርሰን ጋር ተወያይተው በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካካል ያለውን ወታደራዊ ግንኙነት ለማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ አንደነበር ተመላክቷል፡፡

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ሁለቱ ሀገራት የቆየ ግንኙነት ቢኖራቸውም አሁን እያደገ የመጣውን ከፍተኛ የዲፕሎማሲና ወታደራዊ ግንኙነት ወደላቀ ስትራቴጂካዊ የሥራ አጋርነት ማሳደግ ይገባል፡፡

የሁለቱንም ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸው÷ የሁለቱን ሀገራት እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመው÷ አሸባሪነትን ለመዋጋት ከስምምነት መድረሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ታሪክን ለማሰላሰልና የወደፊት ትብብርን ለማጠናከር ትርጉም ያለው አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በአየር ኃይል አከባበር ላይ ለመገኘትና ለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንደገና ለማየትም ዕድል እንደሰጣቸው አብራርተዋል፡፡

ጉብኝቱ በተለይም የጋራ ቀጣናዊ የደህንነት ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እንደገና ለማጠናከር ትልቅ አጋጣሚ ፈጥሯል ማለታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ፡-

Exit mobile version