አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዜጎች በዋትሳፕ፣ በቴሌግራም እና በሌሎች የመልዕክት መላላኪያ አማራጮች ለሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች እና የማጭበርበር ድርጊቶች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል አለ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ)።
ኢመደአ በኢትዮጵያ የዲጂታል ትስስር መስፋፋትን ተከትሎ በዋትሳፕ፣ ቴሌግራም እና በሌሎች ፕላትፎርሞች አማካኝነት በዜጎች ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችና የማጭበርበር ድርጊቶች በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣታቸውን አመልክቷል፡፡
አሁን ላይ በሀገሪቷ የሚካሄዱ የተለያዩ ሲምፖዚዬሞችን፣ ዓለም አቀፍ መድረኮችን እና የኦንላይን ስብሰባዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሳይበር ወንጀለኞች የእነዚህን ኩነቶች ስም ለሀሰተኛ ድርጊቶቻቸው መጠቀሚያ እያደረጉት እንደሚገኙ ጠቁሟል።
እነዚህ አካላት የማሕበረሰቡን የግል መረጃ ለመስረቅ፣ የባንክ ሒሳቦችን ለመመዝበር እና የዲጂታል ደህንነትን ለማናጋት በተቀናጀ መልኩ እየሰሩ መሆኑን አስተዳደሩ በክትትልና በምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
የሳይበር ጥቃቶች የሚፈጸሙት ማህበረሰቡ ትኩረት የሚሰጣቸውን “ተፈላጊ” እና “ወቅታዊ” የሆኑ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ በተዘረጋ ስልታዊ የማታለያ ዘዴ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
አጭበርባሪዎቹ “ለሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች የተዘጋጀ ነጻ የኢንተርኔት ፓኬጅ”፣ “ልዩ የስራ ቅጥር” ወይም “ይህ የስብሰባ መሳተፊያ ሊንክ ነው፤ ከፍተው ይግቡ” የሚሉ አሳሳችና ማራኪ መልዕክቶችን በማሰራጨት ተጠቃሚዎች በመልዕክቱ ውስጥ የተካተተውን ሊንክ እንዲጫኑ ያደርጋሉ፡፡
ይህ ድርጊት ተጠቃሚው ሳያውቀው ወደ አጥፊ ተልዕኮ ወዳላቸዉ ድረ ገጾች እንዲያመራና ለጥቃት ተጋላጭ እንዲሆን የሚያደርግ የመጀመሪያው የወንጀለኞች ርምጃ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ጥቃት አድራሾቹ የአንዳንድ ግለሰቦች የግንዛቤ እጥረትና ትኩረት ማጣት የተነሳ የሚላኩላቸውን ሊንኮችና መልዕክቶች በጥንቃቄ የመመርመር ዕድላቸው አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ ወንጀለኞቹ ይህን ሁኔታ እንደ ምቹ አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
ይህ አይነቱ ጥቃት ከግለሰቦች መረጃ ስርቆት ባለፈ በእጃቸው የሚገኙ ሚስጥራዊ መረጃዎች በጠላፊዎች እጅ እንዲወድቁ በማድረግ በሀገር ደህንነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚጋርጥ መሆኑን አስተዳደሩ በጥብቅ አሳስቧል።
በዚህም ተጠቃሚዎች የተላከላቸውን ሊንክ ሲጫኑ ወይም የተጠየቁትን መረጃ ሲሞሉ፣ የዋትሳፕ ወይም የቴሌግራም አካውንታቸው ወዲያውኑ በጠላፊዎች ቁጥጥር ስር እንዲውል ያደርጋል፡፡
ወንጀለኞቹ አንዴ የአንድን ሰው አካውንት ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ የተጠለፈውን አካውንት በመጠቀም በተጎጂው ስም ለቅርብ ወዳጅ ዘመዶቹና ለስራ ባልደረቦቹ “ድንገተኛ ችግር አጋጥሞኛል” የሚሉ የሀሰት የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄዎችን ይልካሉ።
ይህም ድርጊት በማህበረሰቡ መካከል ያለውን መተማመን ከመሸርሸሩ ባለፈ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በማጭበርበር እንዲመዘበር በማድረግ መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚና የስነ ልቦና ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡
ከላይ የተጠቀሱና መሰል የሳይበር ደህንነት ስጋቶችን ለመቀነስ፣ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም ማህበረሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ኢመደአ አሳስቧል።
ከማይታወቁ ወይም ካልተረጋገጡ አድራሻዎች በዋትሳፕ፣ በቴሌግራም እና በሌሎች መድረኮች የሚላኩ ሊንኮችን ካለመክፈት ባለፈ፣ አጠራጣሪ መልዕክቶች ሲደርሱ ወዲያውኑ “Report” እና “Block” በማድረግ የጥቃቱን ስርጭት መግታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።
በተጨማሪም ማንኛውንም አይነት ሚስጥራዊ የይለፍ ቃል ወይም በስልክ የሚላክ የማረጋገጫ ኮድ ለማንም አካል አለመስጠት ለዲጂታል ደህንነት ወሳኝ መሆኑን አመልክቷል።
አስተዳደሩ እያንዳንዱ ተጠቃሚ በተለይም ማህበረሰቡ በመተግበሪያዎቹ ላይ የሁለትዮሽ ማረጋገጫ (Two-Step Verification) በአስቸኳይ እንዲተገብር መክሯል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እነዚህን የሳይበር ወንጀለኞች በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የጸጥታና የፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
ማህበረሰቡ ማንኛውም የሳይበር ጥቃት ሙከራ ሲያጋጥመው ወይም አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት በነጻ ስልክ መስመር 933 በመደወል ለኢመደአ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።

