አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቴሌብር መተግበሪያ እስካሁን ከ6 ነጥብ 88 ትሪሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ተፈጽሟል አሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፡፡
ፍሬሕይወት ታምሩ የተቋሙን የ2018 የግማሽ በጀት ዓመት አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
በተለይም ዲጂታል የገንዘብ ዝውውርን ከማሳለጥ አንጻር ቴሌብር ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን ነው የተናገሩት።
ዲጂታል ፋይናንስን በማጠናከር ቀልጣፋና ዘመኑን የዋጀ ተደራሽና አካታች አገልግሎት ለመስጠት መሰራቱን አመልክተዋል፡፡
አሁን ላይ የቴሌብር ደንበኞች ቁጥር 58 ነጥብ 61 ሚሊየን መድረሱን ገልጸው፥ በግማሽ ዓመቱ ተጨማሪ 4 ነጥብ 69 ሚሊየን ደንበኞችን ማፍራት ተችሏል ነው ያሉት።
በመንፈቅ ዓመቱ በቴሌብር አማካኝነት 1 ነጥብ 94 ትሪሊየን ብር የገንዝብ ዝውውር መደረጉን ገልጸው÷ አገልግሎቱ ከተዋወቀ ወዲህ እስካሁን በቴሌብር የተፈጸመው የገንዘብ ዝውውር 6 ነጥብ 88 ትሪሊየን ብር ደርሷል ብለዋል።
በቴሌብር የብድር አገልግሎት ከ16 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም አመልክተዋል።
በመላኩ ገድፍ

