አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 8 ሺህ 300 ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ተከታትለው የምስክር ወረቀት ወስደዋል።
የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ስኬታማነት ክልሉ የበኩሉን ሚና ለመወጣት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ለዚህም የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ የተያዘውን የዲጂታል ኢትዮጵያ ዓላማን እውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያበረክት በመሆኑ በክልሉ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሥልጠናውን በመውሰድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ለማስቻል ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
እንደ ሀገር የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ የተለያዩ የግንዛቤ ስራዎችን በመስራት ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው÷ እስካሁን 8 ሺህ 300 ዜጎች ስልጠናውን በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን አመልክተዋል።
ክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት 83 ሺህ 112 ዜጎችን ለማሰልጠን አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን የገለጹት ኃላፊው÷ 28 ሺህ 930 ዜጎች ስልጠናው እየተከታተሉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ስልጠናው በአራት መሠረታዊ ዘርፎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎትና ዕውቀት ለማስጨበጥ ታስቦ እየተሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የስልጠናውን ተደራሽነት ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአድማሱ አራጋው

