ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 ዓ.ም ታህሳስ እና ጥር ወራት ቁልፍ የሆኑ እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሁም ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥሉ ተከታታይ ተግባራትን አከናውነዋል።
በዚህም በሀገር ውስጥ የብሔራዊ የሎጂስቲክስ ክዋኔ፤ ግዙፍ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት፤ ታዳሽ ኃይል የማስፋት ተግባራት እና አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ሐብቶችን በተመለከተ ስኬታማ እንቅስቃሴ አድርገዋል።
ሀገራዊ ጉዳዮች እና ስትራቴጂካዊ የልማት ሥራዎች
የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን በተመለከተ፥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የምሁራን ሚና ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።
እንዲሁም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የክረምት በጎ አድራጎት መርሃ ግብርን ወደ ላቀ ከፍታ ያሸጋገረውን እና በቤተሰብ ደረጃ ለ150 ዜጎች ምቹና ጽዱ መኖሪያ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀውን የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደርን በይፋ መርቀዋል።
በዚሁ ተመሳሳይ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ይፋዊ በሆነ መርሃ ግብር በስፍራው አስጀምረዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ አውሮፕላን ማረፊያው በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፤ በታቀደው መሠረት ሙሉ ግንባታው በሚጠናቀቅበት ወቅት በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ያስተናግዳል።
በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር የኩራት ምንጭ መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፤ ይኽ የሆነው ግን ያለተግዳሮት በመጓዙ ሳይሆን በጽናት በተሞላው እንቅፋቶችን የመሻገር አቅሙ እና በአፍሪካ የፋና ወጊነት ሚናው የተነሳ መሆኑን አስምረውበታል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቁልፍ የመንግሥት ፋይናንስ እና ሌሎች የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማትን ባሰባሰበው የኢትዮጵያ “የፋይናንስ እመርታ” ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው ሀገሪቱ እያካሄደች ስላለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከሚገኙ ሠራተኞች ጋር በዓልን በጋራ አሳልፈዋል።
ደህንነት፣ አቪዬሽን እና ብሔራዊ አቅም ግንባታ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢፌዲሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ በተሰናዳው የአቪዬሽን ኤክስፖ 2026 ይፋዊ የመክፈቻ መርሃግብር ላይ ተገኝተዋል።
እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት አየር ኃይሉ “የጥቁር አንበሳ” የአየር ላይ ትርዒት የተካሄደ ሲሆን፤ ታሪካዊ ሚናውን እና በአሁኑ ጊዜ በተራቀቀ ቴክኖሎጂ የተደገፈውን ከፍተኛ የመፈጸም አቅም በተመለከተ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ በአየር ኃይሉ ተገኝተው በስፍራው ምልከታ ያደረጉ ሲሆን፤ ዝግጁነቱን በመገምግም የኢትዮጵያን የመከላከል አቅም አረጋግጠዋል።
ቱሪዝም፣ የኃይል መሠረተ ልማት እና ዘላቂ እድገት
ጥር ወር በገበታ ለትውልድ መርሃ ግብር አማካኝነት የኢትዮጵያ የቱሪዝም ፖርትፎሊዮ በመሠረታዊነት ጉልህ መስፋፋትን አሳይቷል።
የጥብቅ ደን እና የተፈጥሮ ኃብት ስጦታ የሆነው ደንቢ ኢኮ ሎጅ በይፋ መመረቁ፤ በተለይ ኢኮ ሎጅው የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ባለፉት ሰባት ዓመታት ዘላቂነትን፣ የቅርስ ኃብትን እና ለዘመናት የሚዘልቅ አለም አቀፍ ደረጃን የመጠበቅ እድል መፍጠርን በማዋሃድ ምን ያህል እንደተለወጠ ማሳያ ነው።
በተመሳሳይ የሸበሌ ሪዞርት በይፋ የተመረቀ ሲሆን፤ ሪዞርቱ የገበታ ለትውልድ ዋነኛ ፕሮጀክት ሆኖ በ385 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው፡፡ ሪዞርቱ ምግብ ቤቶች፣ ልዩ የባሕል ማዕከል፣ ዘመናዊ የክብረ-በዓላትና የስብሰባ አዳራሾች፣ የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎችና የእግረኛ መንገዶችን የያዘ በመሆኑ፤ እነዚህ የልማት ስኬቶች ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ በአፍሪካ ቃዳሚ መዳረሻ እንድትሆን ያስችሏታል።
በኃይል ልማት ዘርፍ ደግሞ ኢትዮጵያ የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በይፋ በመመረቅ፤ በታዳሽ ኃይል ላይ አዲስ ታሪክ የጻፈ ታላቅ እጥፋት ከመሆኑም በላይ ሀገሪቱ የኃይል አማራጮችን ለማስፋፋት እና አስተማማኝ ለማድረግ የወሰደችው ወሳኝ እርምጃ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይህ አስተማማኝ የኃይል ልማት በቴክኖሎጂ ለተደገፈ ኢኮኖሚያዊ እድገት መሠረት ይጥላል።
የገጠር ልማት፣ ትምህርት እና ተቋማዊ ማሻሻያ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ ባደረጉት ጉብኝት ሞዴል ገጠር ኮሪደር ስፍራን ተመልክተዋል። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀዳማዊት እመቤት ጋር በመሆን በሱርማ ወረዳ የተገነባ የትምህርት ቤት ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ ታድመዋል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተከናወኑ ማሻሻያዎችን በተቋሙ ተገኝተው የተመለከቱ ሲሆን፤ የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባለፉት ዓመታት ይስተዋሉበት የነበሩ የአገልግሎት ክፍተቶቹን ለማረም የተለያዩ የለውጥ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮ- ጂቡቲ ምድር ባቡር አ.ማ ጉብኝት አድርገዋል። በጉብኝቱ እንደ ደረቅ ወደቦች፣ የባቡር መሠረተ ልማት፣ አውራ ጎዳናዎች እና የመጋዘን ግንባታ አስፈላጊ ማሻሻያዎችና ዘመናዊ የማድርግ ሥራዎች በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግባራት
በዲፕሎማሲያዊው ጎራ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጂቡቲ እና የሶማሊያ መሪዎችን በጅግጅጋ አየር ማረፊያ ተቀብለው አነጋግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ለክልላዊ ትብብር እና መረጋጋት እያሳየች ያለውን ቁርጠኝነት አጉልቶ ያሳያል። እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይን ተቀብለው የወል ፍላጎት በሆኑ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዩናይትድ ኪንግደም የኮመንዌልዝ፣ ልማት ጉዳዮች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቬት ኩፐርን አግኝተው በቁልፍ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ከውይይታቸው ጎን ለጎን በተካሄደው የኢንቨስትመንት አማካሪዎች ማህቀፍ ሥር የኢንቨስትመንት እና ኃብት አስተዳደር የቴክኒካል ትብብር የመግባቢያ ሥምምነት እና የሁለት የጋራ የልማት ስምምነቶች ፊርማ መርሃ ግብር ላይም ተገኝተዋል። እነዚህም የሁርሶ-አይሻ 400 ኪሎ ቮልት እና የደገሃቡር-ቀብሪደሃር 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክቶች ስምምነቶች ናቸው።
በጥቅሉ በታህሳስ እና ጥር ወር 2018 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ስትራቲጂክ ጠቀሜታ ያላቸውን ፕሮጀክቶች በማፋጠን፤ የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን በማስፋፋት፤ የተጠናከረ ብሔራዊ መከላከያ እና የአየር ኃይል እንዲኖር እንዲሁም ንቁ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ተሳትፎ እንዲሳለጥ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ተግባራት የተከናወኑበት ነበር።
ይህም ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊነት፣ ወደ ጸና ሀገራዊ እድገት እና ዘላቂ ብልጽግናን እውን ለማድረግ የጀመረችውን የስኬት ጉዞ በጠንካራ መሠረት ላይ ያስቀመጠ ተግባር ተደርጎ ይወሰዳል።

