አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኑሮ ውድነት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የዜጎችን ገቢ የሚያሳድጉ ተጨባጭ ስራዎች እየተሰሩ ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚስተዋለው የኑሮ ውድነት ችግር አንዱ ምክንያት የምርት ፍላጎትና አቅርቦት መራራቅ መሆኑን ጠቅሰው፥ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ሌላኛው ምክንያት ዜጎች ያላቸውን ውስን ገቢ ለሚያስፈልጓቸው አስገዳጅ ጉዳዮች ወጪ ለማድረግ የሚመጣጠን ባለመሆኑ ገቢያቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
በዚህም ምክንያት መንግስት ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ በተከታታይ የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉን አስታውሰው፥ ዋና ትኩረታችን እዳና ቀንበር ያልተጫነው ሀገርና ትውልድ መፍጠር ነው ብለዋል፡፡
የኑሮ ውድነት ችግሩን ለማቃለል ከደመወዝ ጭማሪና የጡረታ ገቢን ከማሳደግ በተጨማሪ በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለመድሃኒት፣ ለነዳጅና ለአፈር ማዳበሪያ ከፍተኛ ድጎማ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሌላኛው የኑሮ ውድነት አባባሽ ሁኔታ ከግብይት ስርዓቱ ጋር የተገናኘ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በየአካባቢዎቹ የተዘጋጁ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ብዙ ችግር እየፈቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች የተለያዩ ምርቶችን በተሻለ ዋጋ በቀጥታ ከአርሶ አደሩ መሸመት የሚችሉባቸው ትልልቅ ገበያዎች እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ዘመን ገበያን የመሳሰሉ ዲጂታል የግብይት ስርዓቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት በዋጋ ግሽበት የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የበጀት አስተዳደርን ማስተካከል እንደሚገባ በመገንዘብ ከብሔራዊ ባንክ ብድር ሳይወስድ ዓመቱን ማሳለፍ የሚችልበትን ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
እነዚህን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን በማከናወን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋጋ ንረት ወደ ነጠላ አሀዝ መውረዱን ጠቅሰው፥ ወደ 9 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ብሏል ነው ያሉት፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

