አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያን ለመጉዳት ባንዳዎችን በገንዘብ የሚረዱ ኃይሎች ኢትዮጵያን ስለማይችሏት እነሱ ሲከስሩ እኛ ጉዟችንን እንቀጥላለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የእኛ ምርጫ በዘላቂነት ነገን በሚፈውስ ጉዳይ ላይ ማተኮር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለዚህም አንደኛው መፍትሄ በኢኮኖሚ እድገትና በተቋም ግንባታ የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም ማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሀገራዊ ለውጡ ሲመጣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የጦር አውሮፕላኖች አገልግሎት አቁመው ማብረር የሚችለው አንድ ሄሊኮፕተር ብቻ እንደነበር አስታውሰው፥ ዛሬ ከመቶ በላይ ልዩ ልዩ የጦር አውሮፕላኖችን ታጥቋል ብለዋል፡፡
ባንዳ ከማቁሰል አያልፍም፥ ዝግጅታችን ለቁስል ሳይሆን ምሶሶን የሚገዳደር ኃይል ከመጣ ኢትዮጵያን ለማጽናትና ለማስቀጠል ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ጠላቶቻችን ለባንዳ ከሚከፍሉት የበለጠ ሀብት መፍጠር ካልቻልን በገንዘብ፣ በሚዲያና በዲፕሎማሲ ጫና ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ነው የገለጹት፡፡
የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮቿን መፍታት ሳትችል የቀይ ባህርን ጉዳይ ያነሳል የሚል ክስ እንደሚያቀርብ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሆኖም በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ እየገባ የሚገኘውን መሰል ኃይል ከድርጊቱ ለማስቆም መፍትሄው መብቃት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለመጉዳት ባንዳዎችን በገንዘብ የሚረዱ ኃይሎች ስለማይችሏት እነሱ ሲከስሩ እኛ ጉዟችንን እንደምንቀጥል አረጋግጣለሁ ነው ያሉት፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

