Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሀገር ውስጥ የውይይት በር ክፍት ማድረግ አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር ውስጥ የውይይት በር ክፍት ማድረግ አለብን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ነው።

በሀገር ውስጥ የውይይት በር ክፍት ማድረግ አለብን፤ ዛሬ ባንዳ የሆነ፣ ከኢትዮጵያ ተቃርኖ የቆመ ሰው ልብ ገዝቶ በቃኝ ካለ ሁሌም ክፍት መሆን አለብን ብለዋል፡፡

በሀገር ጉዳይ ቂም መያያዝ አያስፈልግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ልቤ ታድሷል፤ አዕምሮዬ ተቀይሯል ካለ በራችን ክፍት መሆን አለበት በማለት ገልጸዋል፡፡

ጉዳያችን ኢትዮጵያን የሚጠቅም ከሆነ በይቅርታ ለማለፍ ዝግጁዎች ነን፤ በዚህም በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ታጣቂዎች ተመልሰው እየገቡ ይገኛሉ ብለዋል በማብራሪያቸው።

ለሰላም ዝግጁ እስከሆነ ድረስ የግል ስሜትን ወደጎን በመተው ለይቅርታ ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

ብሔራዊ ጥቅም ላይ አሁን ያለው ሁኔታ መሻሻሉን ገልጸው÷ በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የተቃረነ እንቅስቃሴን በመቃወም ወደ ሰላም እየመጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በጫካ ሆነው ከመንግሥት ጋር ትብብር እያደረጉ የሚገኙት ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም ሲሉም አስረድተዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version